በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት እና ከትምህርት ገበታ ሆን ብሎ መቅረት

የትምህርት ቤት ቀሪ መቆጣጠሪያ፣ ከትምህርት ቤት መቅረት እና በትምህርት ገበታ አለመገኘት

“Becca Bill” (ቤካ ቢል) በመባል የሚታወቀው የዋሽንግተን የስቴት ሕግ ዕድሜያቸው በ 8 እና 18 መካከል ያለ ሕፃናት በመደበኛነት ትምህርት ቤት ገብተው መማር እንዳለባቸው ይደነግጋል።ሕጉ ወላጆችን ወይም ሕጋዊ ሞግዚቶችን ልጆቻቸው በመደበኛነት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ስለ መሆናቸው እንዲያረጋግጡ ያስገድዳል።ተማሪዎች በሕዝብ ትምህርት ቤት፣ በግል ትምህርት ቤት ወይም በቤት ውስጥ ትምህርት ቤት ገብተው መማር ይችላሉ።ሕጉ አሳማኝ የሆነ ምክንያት ከሌለ በቀር ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ፣ ሙሉ ቀን፣ በየቀኑ መገኘት እንዳለባቸው ያስገድዳል።አንድ ተማሪ ያለ በቂ ምክንያት ከትምህርት ቤት ሳይገኝ ቢቀር፣ ተማሪው እንደ “ሆን ብሎ ከትምህርት ገበታ የሚቀር” ተማሪ ተደርጎ ይቆጠራል። አንድ ተማሪ ሆን ብሎ ከትምህርት ገበታ ይቀራል ከተባለ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲህ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል፦

  • ለቤተሰቦች ማስታወቅ፤
  • ለምን እንዲህ እንደሆነ ለማወቅ ከቤተሰብ እና ከተማሪው ጋር ተገናኝቶ አብሮ መወያየትና መፍትሔ መፈለግ፣ እና
  • የተማሪውን በትምህርት ገበታ የመገኘት ሁኔታን ለማሻሻል እንዲያግዝ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም።

ይህ ምንም ውጤት ካላስገኘ፣ ተማሪው እና ቤተሰቡ ወደ Community Truancy Board (የማኅበረሰብ ከትምህርት ገበታ ሆን ብሎ መቅረት ችግር አጣሪ ቦርድ) ወይም ወደ ፍርድ ቤት ሊላኩ ይችላሉ።አንድ ተማሪ፣ ከአሳማኝ ምክንያትም ጋር ቢሆን ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ከትምህርት ቤት ከቀረ፣ አሁን ላይ ሕጉ ትምህርት ቤቶች ችግሩ ለምን እንደተፈጠረ ለማወቅ እና ተማሪው በመደበኛነት ወደ ትምህርት ገበታው መመለስ እንዲችል የመፍትሔ ዕቅድ ለማዘጋጀት ከወላጆች ጋር እንዲገናኙ ያስገድዳል።  ይህ የሆነበት ምክንያት ከትምህርት ቤት ደጋግሞ መቅረት ወይም “ሥር የሰደደ ከትምህርት ቤት የመቅረት አባዜ” ተማሪው ትምህርቱን በሚገባ መከታተል እንዳይችል ስለሚያደርገው ነው።ከዚህ በተጨማሪ ተማሪው ማግኘት የሚያስፈልገውን ድጋፍ እያገኘ እንዳልሆነ ጠቋሚ ምልክት ሊሆን ይችላል።ስለ ከትምህርት ቤት መቅረት ስናወራ፣ “ብዙ” ማለት እንደ “ትንሽ” ሊመስል ይችላል – በወር 2 ቀን ብቻ ከትምህርት ገበታ ላይ አለመገኘት በራሱ ትልቅ ተፅዕኖን ሊፈጥር ይችላል! 

ልጅዎን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ላይ በየቀኑ አስቸጋሪ ከሆነብዎት፣ ትምህርት ቤትዎ እንቅፋቱን እንዲያስወግዱ ሊያግዝዎት እና የእርስዎንም ልጅ በየቀኑ፣ ሙሉ ቀን፣ ሰዓቱን አክብሮ በትምህርት ቤት የመገኘት ልማድን እንዲያጎለብት ሊያግዘው ይችላል። አንድ ተማሪ ከትምህርት ገበታው መቅረቱን ከቀጠለ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል እና ወደ መደበኛ የትምህርት ገበታ ላይ የመገኘት ልማድ ለመመለስ ስለሚያግዙ ሐሳቦች ለማወቅ የ OEO ተዘውትረው የሚጠየቁ ጥያቄዎችን ይመልከቱዋቸው። በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ላይ ስላለ ችግር ተጨማሪ እገዛ ካስፈለግዎት፣ እባክዎ ስልክ ይደውሉ!የእኛን የድር ጣቢያ እዚህ https://oeo.wa.gov/am ላይ ይጎብኙ ወይም 1-866-297-2597 ላይ ይደውሉ።

ሕጉ ትምህርት ቤቶችን ምን ያስገድዳቸዋል?

  • ስለ በትምህርት ቤት የትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ስለ ተቀመጡት ደንቦች ለወላጆች ማስታወቅ እና ማስታወቂያው እንደደረሳቸው ለማሳየት ፊርማቸውን ማግኘት
  • ተማሪ ከትምህርት ቤት በቀረ ቊጥር ለወላጆች ማስታወቅ፣
  • ለምን እንደሆነ ለማወቅ ከወላጆች እና ከተማሪው ጋር ተገናኝቶ መነጋገር፣
  • በትምህርት ገበታ ላይ የመገኘት ሁኔታን ለማሻሻል የተለያዩ ዘዴዎችን መሞከር፣ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች፣
  • ተማሪውን እና/ወይም ቤተሰቡን ወደ Community Truancy Board መላክ።

ሕጉ ተማሪዎችን ምን ያስገድዳቸዋል?

  • በትምህርት ቤት ውስጥ፣
  • በጊዜ ሳያረፍዱ፣
  • አሳማኝ የሆነ ምክንያት ከሌለ በቀር በየቀኑ።